
በክልሉ ሁሉም ተቋማት ወረቀት አልባ አገልግሎት ለማቅረብ በሚያችላቸው ሲስተም ዝርጋታ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ። (ሆሳዕና፣ ሚያዚያ 17/2017)፣ የቢሮው የ9 ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በዱራሜ ከተማ እየተካሄደ ነው። በክልሉ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ አገልግሎት ለማቅረብ በሚያችላቸው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሲስተም ዝርጋታ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታውቋል ። ሴክተሩ ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጣሉበትን ሃላፊነቶች ለመወጣት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተቀናጀ መንገድ ጥረት ማድረጉንም ጠቁሟል። የቢሮው ሃላፊ ሰላሙ አማዶ የሴክተሩ የ9 ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በዱራሜ ከተማ ሲካሄድ እንዳሉት ቢሮው ተቋማት ከወረቀት ንክኪ ነጻ፣ ፈጣንና የተገልጋይን ጊዜና ወጪ ለመቀነስ በሚያስችላቸው ሲስተም ዝርጋት ግቦችን አስቀምጦ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። ይህን መሰረት አድርጎ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ተቋማት አስራ አምስት ሲስተሞች የለሙ ሲሆን 15 ሲስተሞችን የመዘርጋት ተግባር መከናወኑን አቶ ሰላሙ አስታውቀዋል። በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ብቃት ማረጋገጥና ፈቃድ እድሳት፣ በዘርፉ መሳሪያዎች ጥገና፣ የሳይንስ ፈጠራ ስራዎችን በመደገፍና ወደ ተግባር በማስገባት ረገድ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን የቢሮ ሃላፊው ተናግረዋል።