Skip to main content
zena35

ለኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ውጤታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ተገለፀ!(መጋቢት 29/2017 ቡታጅራ) መንግስት ለሁሉም ዜጎች ለማድረስ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ያስጀመረውን የ 5 ሚሊዮን ሰልጣኞች ኢትዮ ኮደርስ ኢንሼቲቭ ስልጠና ውጤታማ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ፤ የኢቲዮ ኮደርስ ስልጠና አስተባባሪ አብይ ኮሚቴው በ9 ወር ውስጥ የነበረውን የአፈፃፀም በጥልቀት ገምግሟል። የምስራቅ ጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ሃላፊ እና የአብይ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ደሱ አበጋዝ " መንግስት በአጋር አካላት ድጋፍ 5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደርስ የስልጠና እድል አዲስ ኢኒሼቲቭ ሲያስጀምር ያለምንም ክፍያ በነፃ እንደ ኢትዮጵያ በሶስት አመታት ውስጥ 5 ሚልዮን ኮደርስ ለመሰልጠን ሲሆን እንደ ዞናችን ደግሞ ከ 15,572 በላይ ኮደሮችን ነጻ የኦንላይን ሥልጠና እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመስራት የታቀደ ሲሆን ከአመራሩ ጀምሮ ሁሉም ለውጤታማነቱ በትጋት ሊተባበር እንደሚገባም አስታውቀዋል። የምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊና የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሠልማን ሳኒ በበኩላቸው " ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ ከፍታ በምታደርገው የቴክኖሎጂ ዲጂታል ዓለም ጉዞ አጋዥ አንዲሆን ያስጀመሩት ይህ ነፃ የ 5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ሁሉም በቅንጅት በመስራት ውጤታማ ሊያደርገው ይገባል ብለዋል። የምስራቅ ጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ልኬለሽ ከበደ ይህ 5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከአይሲቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ኮርሶች በኦዳሲቲ ፕላትፎርም (Udacity Platform) የፕሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስ፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስና ሌሎችም ከአይሲቲ ጋር የተገናኙ ኮርሶችን ከክፍያ ነፃ ማግኘት የሚያስችል መሆኑን በማስረዳት፤ በዚህ ስልጠና ተመዝግበውና የትምህርት ይዘቶቹን ተምረው ያጠናቀቁ ተሳታፊዎች በአለም አቀፍ ድርጅቶች እውቅና ያለው እና የስራ እድልን በእጅጉ ሊያሳድግ የሚችለውን Udacity የምስክር ወረቀት እንደሚሰጣቸውም አስታውቀዋል። አያይዘውም የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የ9 ወር አፈፃፀም አስመልክተው ባቀረቡት ሰነድም እንደ ዞን በ2017 በጀት ዓመት 3893 ኮደርስ ለማሰልጠን ታቅዶ ከምዝገባ አንፃር የእቅዱ 78% ማከናወን መቻሉን የገለፁ ሲሆን ስልጠናውን ጨርሰው ሰርተፊኬት የወሰዱት 24% ብቻ ናቸው።በመሆኑም በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት እቅዱን ለማሳካት ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የአብይ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ይህ ስልጠና መንግስት ለዜጎች በነፃ ቢያቀርበውም እንደ ሀገር ከፍተኛ ወጪ የወጣበት በመሆኑ ሁሉም በትጋት ሰልጥኖ የነገዋ የበለፀገችዋ ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ይገባዋልም ብለዋል። በመጨረሻም የኢትዮ ኮደር ስልጠና ለመውሰድ www.ethocoders.et ብሎ በመግባት ያለ ምንም ኢንተርኔት ክፍያ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናው መሠልጠን እንደሚቻልም ተጠቁሟል።