
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 40ሺ ዜጎች በኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ተጠቃሚ መሆናቸው ተመላከተ በክልሉ በ5ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገብ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደገለጹት ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል። ፕሮግራሙ ትውልድን ለሚቀጥለው ጊዜ በእውቀት ማበልጸግን ያለመ ስለመሆኑም ኃላፊው አመላክተዋል። የወጣቶችን ዲጂታል ክህሎት በማጎልበት በአለም ከሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ስለመሆኑ የተናገሩት አቶ ሰላሙ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት የተገኘነውን እድል ወደ ውጤት መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። በክልሉ በኢትዮ ኮደርስ ለ198ሺ 284 ዜጎች ስልጠና እንዲያገኙ እድል ተሰጥቷል ያሉት ኃላፊው እስካሁን ባለው አፈጻጸም 40ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች በስልጠናው መሳተፋቸውን ጠቁመዋል። በክልሉ 17ሺ 844 የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠናቸውን አጠናቀው ሰርተፍኬት ማግኘታቸውን አብራርተዋል። በዲጂታል ክህሎት የበለጸገ ማህበረሰብ በመፍጠር ሂደት ስልጠናው ወሳኝ ነው ያሉት ኃላፊው የተገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ስለመሆኑም አመላክተዋል። ስልጠናው የዜጎች የቴክኖሎጂ ክህሎት ከማሳደግ ባለፈ በስራና በሀብት ፈጠራ ላይ የሚኖረው ድርሻ የላቀ ስለመሆኑም አመላክተዋል። በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ፣በክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ዋሌራ፣ከክልል፣ከዞን እና ከልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አመራሮች ተገኝተዋል።