
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ እና የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን ማብቃት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጁት መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው። (ሆሳዕና፣ የካቲት 05/2017)፣ቢሮዎቹ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን ከክልላዊ የልማት ፕሮግራሞች እንዲሁም ከዘላቂ የስራ ዕድል ፈጠራ ጋር አስተሳስሮ ለማስተግበር በቅንጅት እንደሚሰሩ ተገልጿል። በ2016 በጀት ዓመት በተዘጋጀው የፈጠራ ውድድርና ኤግዚቢሽን የቀረቡ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን በማሻሻል ወደ ማህበረሰቡ ለማሻገር ቢሮው ከክልሉ ቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። ስለሆነም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች በየመዋቅሩ ከሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር በማስተሳሰር የማቴሪያልና ቴክኒካል ድጋፍ በማግኘት የተሻለ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ማብቃት የሚያስችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይቱ የሚደረግ ስለመሆኑም ተመላክቷል። በመድረኩ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሁለቱም ቢሮዎች ማኔጅመንትና የመዋቅር ኃላፊዎች ፣ከዋቸሞ፣ ወልቂጤና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ እንግዶች፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲኖች እንዲሁም የፈጠራ ባለቤቶች ተገኝተዋል።