
የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ፍትሀዊ ውድድርን በማስፈን ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር በአዕምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ዙሪያ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ እየተሰጠ ነው። ስልጠናውን በንግግር ያስጀመሩት የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንደገለጹት የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነትን ማረጋገጥ የፈጠራ ሥራዎችን በማበረታታት፣ ፍትሀዊ ውድድርና ተጠቃሚነትን በማስፈን ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝና አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። ዘርፉ ለፈጠራና ግኝት ባለቤቶች የአዕምሮ ንብረት መብት በማረጋገጥ ከማበረታታት ባሻገር ለተጠቃሚውም የምርት ጥራት መረጋገጫ በመሆኑ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጉዳይ በግንዛቤና ክህሎት እጥረት ምክንያት ተገቢው ትኩረት ሳይጠው መቆየቱን ያነሱት ቢሮ ኃላፊው ለዚህም ስልጠናው በጉዳዩ ምንነት፣ አስፈላጊነትና አሠራር ግንዛቤ ለመፍጠር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። ስልጠናው ክልሉን የሳይንስ ኢኖቨሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ ቢሮው የጀመረውን ስራ በጉልህ የሚያጎለብት በመሆኑ በትኩረት እየተመራ መሆኑንም አቶ ሰላሙ አክለዋል። የአዕምሯዊ ንብረት የቅጂ መብት፣ የፈጠራ ስራዎች፣ የንግድ ምልክቶች፣ የኢንዱስትሪ ዲዛይኖች፡፣ ጂኦግራፊያዊ አመላካቾችና ሌሎችንም የአዕምሯዊ ንብረቶችን መብት ጥበቃ የሚያደርግ የህግ ማዕቀፍ መሆኑም ተመላክቷል። ከስልጠናው ጋር በተያያዘ መርሃ-ግብር በክልሉ የመጀመሪያ የሆነ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ድጋፍ ማዕከልን በይፋ ሥራ ማስጀመሪያ ፕሮግራምም ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። በመድረኩ የዞንና የልዩ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።